የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍል በዘመናዊ የሀብት ምዝገባ መረጃ ስርዓት፣ በፌዴራል የስነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እና በተሻሻለው የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ዙሪያ ለኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሠራተኞች ስልጠና ሠጥቷል፡፡

የዘመናዊ የሀብት ምዝገባ መረጃ ሥርዓትን አስመልክተው ስልጠና የሰጡት በፌዴራል የስነምባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ መቅደስ ይትባረክ እንደገለፁት ሲስተሙ ጊዜን፣ ወጪንና ጉልበትን ለመቆጠብ፣ መረጃን በቀላሉ ለመቆጣጠር ፣ሚስጥራዊነቱን ለመጠበቅ፣ ስራን ማዕከል ያደረገ ምደባ ለመስጠት ዓላማ ያደረገ መሁኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ አሰልጣኟ ማብራሪያ የህዝብ ተመራጮች፣ ተሻሚዎችና ሠራተኞች ሀብታቸውን ማስመዝገብ የሚችሉ ሲሆን ወሲስተሙ የሚገቡ የሀብት ዓይነቶች ደግሞ የሚንቀሳቀስና የምይንቀሳቀስ ሀብት፣ እዳ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የምዝገባ ዓይነቶችንና በድጂታል እንዴት መመዝገብ እንደሚቻል ወ/ሮ መቅደስ ጨምረው ያብራሩ ሲሆን ሁሉም ለተግባራዊነቱ መተባበር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል የፊዴራል የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1236/2013 በኢንስቲትዩቱ የስነምግባር መከታተያ ክፍል ዳይሬክተር በአቶ አሰፋ ተስፋዬ እንዲሁም የተሻሻለው የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 18/2013 ደግሞ በክፍሉ የሙስና ስጋት ተጋላጭነት ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት በአቶ አሻግሬ አለነ ቀርበዋል፡፡
ከሰልጣኞች መካከል አንደንዶቹ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የሀገራቸውን እድገት የሚፈታተነውን ሙስና የሚባል ጠላት ለመዋጋት የተሻለ አቅም የፈጠረ ነው፡፡ በመሆኑ ሀብታቸውን በማስመዝገብና እራሳቸውን ከዚህ ድርጊት በማራቅ ሌሎችም ሙስና ሲፈፅሙ በማጋለጥ የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
Comments(0)