Message From Our Director

Abdu Abagibie (D.r)

በሀገራችን በንግዱ ዘርፍ እየተሳተፉ የሚገኙና ወደፊትም የሚፈጠሩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ እንዱስትሪዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ የዜጎች ጤና፣ ደህንነትና ጥቅም እንዲጠበቅ እንዲሁም በሀገሪቱ ዉስጥ የሚካሄዱ የፈጠራ፣ የጥናትና የምርምር ሥራዎቸ ዉጤታማ እንዲሆኑ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት መኖርና መጠናከር ትልቅ ድርሻ ስላለዉ የዘርፉን ሥራ ከማጠናከር አኳያ መንግሥታችን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ብሔራዊ የሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት (ብሥኢ) በሀገሪቱ ዉስጥ ካሉት የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት አንዱ ሲሆን በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 194/2010 ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ የሀገሪቱን የሥነ-ልክ እና የሳይንስ መሳሪያዎች አጠቃቀም ፍላጎት ያሟላ፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለዉ፣ በአፍሪካ ግንባር ቀደምና ተአማኒ ተቋም የመሆን ራዕይ ሰንቆ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በሁለት ዘርፎች ማለትም በሥነ-ልክና በሳይንስ መሳሪያዎች ዘርፍ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሥነ-ልክ ማለት የአለካክ ሳይንስና ትግበራ ማለት ሲሆን ለሳይንስ መሳሪያ የሚሰጠው ትርጓሜ እንደሀገራት የዕድገት ደረጃና ተጨባጭ ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም የሳይንስ መሳሪያ ማለት ለምርምርና ሥርፀት፣ ለትምህርትና ሥልጠና፣ ለጥራት ቁጥጥርና ፍተሻ፣ ለሥነ-ልክ፣ ለሰው ወይም ለእንስሳት ህክምና አገልግሎቶች ሥራ ላይ የሚውል መሳሪያ ማለት ነው:: ልኬት የሰዉ ልጅ ጥንት ይኖርበት ከነበረው ዘላንነት ተላቆና በመንደር ተሰባስቦ መኖር ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በተለያዩ ሀገሮች ወጥ ባልሆኑና በተዘበራረቁ መንገዶች ይተገበር እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ ይህንን የአለካክ መንገድ ወጥና ዘመናዊ የሚያደርግ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ1791 በፈረንሳይ አገር የተመሰረተ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባር ላይ የዋለው እ.አ.አ ከሜይ 20/1875 ጀምሮ ነዉ፡፡ ሀገራችንም እ.አ.አ ከ1963 ዓ.ም. ጀምሮ የሥነ-ልክ ሥርዓትን ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ በዚህ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እጅጉን ወደላቀ ደረጃ በደረሰበትና ተለዋዋጭነቱ አጀብ በሚያስብልበት የምድራችን የዕለት ከዕለት ውሎ ውስጥ የልኬት ሳይንስንና የሳይንስ መሳሪያዎችን አጠቃቀም ጠለቅ ብሎ መገንዘብ እጅግ አስፈላጊ ነዉ፡፡ በመሆኑም የልኬት ሳይንስና የሳይንስ መሳሪያዎች አጠቃቀም በአገራት ዕድገትና መፃኢ ዕድል ላይ ያላቸውን ኃያል ተጽዕኖ የተገነዘበው ብሥኢ የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ በአለካክ መስኮች ዓለም አቀፍ እውቅና እና ተወዳዳሪነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ወጥነት እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የአለካክ ሥርዓት ከመዘርጋት፣ የመለኪያ መሳሪያዎች ትክክለኛነትና የዓለም አቀፍ ደረጃዎችን መጠበቃቸውን ከማረጋገጥ፣ ከሳይንስ መሣሪያዎች አመራረጥ፣ አያያዝ፣አጠቃቀምና አወጋገድ እንዲሁም የጥገና አገልግሎትና በዘርፉ ሥልጠና ከመስጠት፣ በጥናትና ምርምር በማስደገፍ በሥነ-ልክ ዘርፍ የአለካክ ወሰኖች የአገልግሎት ወሰን ሽፋንን ከማስፋት፣ ከማሳደግና አዳድስ የአለካክ መስኮችን ከመክፈት እንዲሁም በሳይንስ መሣሪያዎች ዘርፍ ዘመናዊ የመሳሪያዎች አጠቃቀም ቴክኒኮችን ወደ ሥራ ከማስገባት አኳያ አገልግሎት እየሰጠና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማመጣት እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢንስቲትዩቱ ከዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ፣ አቻ የስነ-ልክ ተቋማት፣ ከባለድርሻ አካላት እና የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅትና በትብብር በመሥራት፣ አህጉራዊ የእርስበርስ ንጽጽር እና ዓለም አቀፍ እርከን ተዋረድ ትስስር ሥራዎችን እንዲጠናከሩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ይንቀሳቀሳል፡፡ የግል ባለሀብቱና የመንግስት ድርጅቶች የራሳቸውን የካሊብሬሽን ላቦራቶሪ እንዲሁም የሳይንስ መሳሪያዎች የጥገና ወርክ ሾፕ እንዲያቋቁሙ ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ከዚህም ሌላ የሥነ-ልክ ትምህርት በቴክንክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ እንዲገባ ብሎም አንዲተገበር ድጋፍ በመስጠት የሀገራችንን ፈጣን ዕድገትና ለወጥ ለማረጋገጥ ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በልኬት ሳይንስም ሆነ በሳይንስ መሳሪያዎች ዘርፍ የተሰለፋችሁ የኢንስቲትዩታችን ሰራተኞችም ሆናችሁ ሌሎች በነዚህ ዘርፎች የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲጠናከሩና የተሳለጡ እንዲሆኑ ሙያዊና አስተዳደራዊ ድጋፍ መስጠት የሚጠበቅባችሁ ሲሆን ከተቋማችን አገልግሎት የምታገኙ ደንበኞቻችንና አጋር ድርጅቶች በተቋማችን የሚሰጡ አገልግሎቶች የአገርና ሕዝብን ጥቅም በሚያስጠብቅና ደህንነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲከናወኑ የበኩላችሁን ድጋፍ እንድታደርጉ ጥሪዬን እያቀረብኩ ይህ ድህረ-ገጽ ኢንስቲትዩቱ የቆመለት ዓላማና የሚያከናዉናቸዉ ዋና ዋና ተግባራት፣ የሀገሪቱን የሥነ-ልክ ፍላጎት ለማሟላት እያደረገ ያለዉን ጥረት እና ሌሎች የኢንስቲትዩቱ የሥራ እንቅስቃሰዎች እንዲሁም ጠቃሚ መረጃዎች የሚቀርብበት ስለሆነ በድህረ-ገጻችን ላይ የምናሰራጫቸውን መረጃዎች እንድትጠቀሙ እንዲሁም አስተያየቶችና ሌሎች መልዕክቶችም ካሉ እንድትገልፁልን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

Abdu Abagibie (D.r)

National Metrology Inistitute Director General

Upcoming Events

Our Events

Our partners